የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው 5ኛ ዓመት 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ያጸደቀውን የምክትል ዋና ኮሚሽነር እና የዘርፍ ኮሚሽነሮች ሹመት በደስታ ይገልጻል። እነዚህ ሹመቶች በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) መሠረት፣ በገለልተኛ አስመራጭ ኮሚቴ አማካኝነት ግልጽ የሆነ የሕዝብ ጥቆማና የመመልመያ ሂደትን ተከትለው የተሰጡ ናቸው።
በዚሁ መሠረት ዶ/ር ሚዛኔ አባተ ታደሰ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር በመሆን ተሹመዋል። ዶ/ር ሚዛኔ አንጋፋ የሰብአዊ መብቶች ምሁር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ሕግ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፤ በሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ በተቋማዊ ሪፎርም እና በሕግ ትምህርት ረገድ ሰፊ ልምድ አላቸው። በኢሰመኮ ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የአመራር ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ በቅርቡም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ በመሆን በፖሊሲ ልማት እና በተቋማዊ ግንባታ ረገድ ጉልህ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
አቶ በዳሳ ለሜሳ ከበደ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ሥልጠና ኮሚሽነር በመሆን ተሹመዋል። አቶ በዳሳ በሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ በምርመራ እና በተቋማዊ አመራር ሰፊ ልምድ ያላቸው አንጋፋ ባለሙያ ናቸው። በቅርቡ በኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ ከፍተኛ ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን የሙያ ብቃታቸው የኮሚሽኑን የሥራ ክንውን እና የአሠራር ሥርዓቶችን በማጠናከር ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
አቶ መሐመድ አሕመድ ሐሰን የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር በመሆን ተሹመዋል። በፍትሕ እና በሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ከ18 ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ ያላቸው ሲሆን በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ የሪጅን ዳይሬክተር፣ በአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት ከማገልገላቸውም በላይ፤ በፍትሕ ሥርዓት፣ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና በተቋማዊ ሪፎርም ረገድ ያላቸውን ጥልቅ ዕውቀት እና ተሞክሮ ወደ አዲሱ ኃላፊነታቸው ይዘው መጥተዋል።
ኢሰመኮ በተመሳሳይ መልኩ ወይዘሮ አሸነፈች አበበ አልቢን የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር በመሆን መሾማቸውን ይገልጻል። ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነት የመጡት ወይዘሮ አሸነፈች፤ በዳኝነት፣ በዐቃቤ ሕግነት እና በሕግ ባለሙያነት ያገለገሉ አንጋፋ የፍትሕ ዘርፍ አመራር ናቸው። በተለይም ሕፃናትን ማዕከል ያደረገ የፍትሕ ሥርዓትን በማሳደግ፣ የሕፃናት ተስማሚ ችሎቶችን በማቋቋም እና የሴቶችንና የሕፃናትን መብቶች በማስከበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ለተሿሚዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ “የምክትል ዋና ኮሚሽነር እና የዘርፍ ኮሚሽነሮች መሾም የኮሚሽኑን አመራር ለማጠናከር የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው” ብለዋል። አክለውም “የኮሚሽኑን ተልዕኮ በጥልቀት የሚረዱ አንጋፋ ባለሙያዎች በእነዚህ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ መሾማቸው የተቋማዊ ዐቅማችን ማሳያ በመሆኑ ልዩ ደስታ ይሰጠኛል። ይህም የኢሰመኮን የአሠራር ቀጣይነት እና የተሳለጠ ሽግግር ከማረጋገጡም በላይ፣ ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም እንዲኖረን ያስችላል። በተመሳሳይ አዳዲስ ዕይታዎችን እና ልምዶችን ይዘው የመጡ አመራሮችን በመቀበላችን ደስተኞች ነን። ይህ ቡድን በጋራ በመሆን ሰብአዊ መብቶችን ለሁሉም ሰዎች የማክበር እና የማስከበር ተልዕኳችንን ያሳካል” ሲሉ ገልጸዋል።