የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያደራጀውን የወቅታዊ ሁኔታ መከታተያ ሥርዓት (Situation Room) ግንቦት 14 ቀን 2018 ዓ.ም. አስጀምሯል፡፡ በመርኃ ግብሩ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮች፣ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት (GIZ – Deutsche Gesellschaft für Internationale Zusammenarbeit) ተወካዮች ተገኝተዋል።


ኢሰመኮ በተሻሻለው የመቋቋሚያ አዋጁ መሠረት በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታን የመከታተል ኃላፊነትና ሥልጣን በግልጽ የተሰጠው ሲሆን፣ የሁኔታ መከታተያው የምርጫው ሂደት ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ መሆኑን ለመከታተል የሚያግዙ ስልቶች እና አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ግብአቶች የተሟሉለት ነው፡፡
የምርጫ ሂደት ሁኔታ መከታተያውን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እና የጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ዳይሬክተር ዶሮቴ ሃተር መርቀው ከፍተውታል።




የሁኔታዎች መከታተያው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና አሳሳቢ ጉዳዮችን በተመለከተ መረጃዎችን በፍጥነት ለማእከል እንዲደርሱ በማድረግ መፍትሔ ለማሰጠት የሚደረገውን ጥረት የሚያሳልጥ ነው። ይህም የምርጫው ሂደት አግባብነት ባላቸው አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሠረት ሰብአዊ መብቶችን አክብሮ መከናወኑን ለማረጋገጥ፣ ማናቸውም ዐይነት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ አስቀድሞ ለመከላከልና ከተፈጸሙም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ፈጣን ምላሽ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር፤ የሰብአዊ መብቶች አንድምታ ያላቸው ከምርጫ ጋር የተያያዙ የጸጥታ ሁኔታዎችን፣ የቴክኒክ ችግሮችን ወይም ሌሎች እንቅፋቶችን በወቅቱ በመረዳት እልባት ለመስጠት እንደሚጠቅም ተብራርቷል፡፡

የጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ዳይሬክተር ዶሮቴ ሀተር የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራዎች መጠናከር ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፣ ለምርጫው ልዩ ትኩረት መስጠቱን በማድነቅ ተቋማቸው አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ እና ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የምርጫ ወቅታዊ ሁኔታ መከታተያው ከፍተኛ ዐቅም በመፍጠር እና በየአካባቢው የሚሰማሩ የክትትል ባለሙያዎች ባሉባቸው ቦታዎች ቀጥታ መረጃ በመስጠት ለውሳኔ የሚረዳ ዐውድ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም መሰል የቴክኖሎጂ ዐቅም በመፍጠር ረገድ የጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት ላበረከተው አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበዋል።