የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) አቶ እስክንድር ነጋ የሚገኙበትን ሁኔታ ለማጣራት ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማረፊያ በመገኘት፣ አቶ እስክንድር ነጋን፣ ክስተቱ ሲፈጠር በስፍራው የነበሩትን አቶ ስንታየው ቸኮልን፣ ከአቶ እስክንድር ጋር ተጋጩ የተባሉትን እስረኛ፣ እንዲሁም የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር አካላት አነጋግሯል።
በማጣራቱ ሂደት ለመረዳት እንደተቻለው፣ አቶ እስክንድር የፍርድ ቤት ቀጠሮ በነበራቸው ሐሙስ ጥቀምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠዋት በሚገኙበት ዞን ግቢ ውስጥ የስፖርት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እያሉ፣ ከዚህ ቀደም እርሳቸው ባሉበት ዞን ታስረው የነበሩና ከዞኑ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተዘዋውረው ከነበሩ ከሌላ እስረኛ ጋር ሲገናኙ በመካከላቸው የተነሳው የቃላት ልውውጥ ወደ አካላዊ ግጭት ተሸጋገረ። ክስተቱ እንደተፈጠረ የእስር ቤቱ ጥበቃዎች እና ሌሎች ታራሚዎች እንዳገላገሏቸውና የማረሚያ ቤቱ አስተዳደርም ሌላኛውን እስረኛ ወዲያው ወደ ሌላ ዞን ማዘዋወሩን ለማረጋገጥ ተችሏል። በአቶ እስክንድር እና በእስረኛው መካከል ከዚህ ቀደም አለመግባባት እንደነበረና እስረኛው ከተዘዋወሩበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በቅርቡ የተመለሱ መሆኑንም ኮሚሽኑ መገንዘብ ችሏል።
በሁኔታው አቶ እስክንድር በግራ እግር አውራጣታቸው ላይ እብጠት፣ በሁለቱም ጉልበቶቻቸው ላይ የመላላጥና በቀኝ ቅንድባቸው ላይ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ በማረሚያ ቤቱ ክሊኒክ የተመላላሽ ሕክምና እያገኙ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አረጋግጧል። በሌላኛው እስረኛ ላይም በቀኝ እጅ ጣቶቻቸው ላይ የመፋፋቅ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማየት ተችሏል።
ሁለቱም ታሳሪዎች በግጭቱ በደረሰባቸው ጉዳት ተገቢው የማጣራት እና የሕክምና ድጋፍ ከማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አካላት እንደተደረገላቸው የገለጹ ሲሆን፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ክስ ለመመስረት ፍላጎት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡
አቶ እስክንድር የተፈጠረው ክስተት ተራ ጠብ ነው ብለው እንደማያምኑና በፍርድ ቤት የምስክር ማሰማት ሂደት እያነሷቸው ባሉ መስቀለኛ ጥያቄዎችና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። በእለቱም በፍርድ ቤት ያልተገኙት ክስተቱ ባሳደረባቸው ስሜት በወሰዱት የግል ውሳኔ እንደሆነና፣ አሁንም ከደህንነታቸው ጋር በተያያዘ ቀጣይ ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል።
ኢሰመኮ ከማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት፣ የታሳሪዎችን ደህንነት ስለማረጋገጥ፣ እንዲሁም በእስረኞች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችና ፀቦችን መከላከልና በሚከሰቱበት ጊዜ ፈጣን እርምጃዎችን መውሰድ የታሳሪዎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አንዱ አካል እንደሆነና፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎች ላይ ተመካክሯል ።