የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ፣ ሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች እና የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮችና አባላት ጋር የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ በማካሄድ ላይ ነው።
ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የሰብአዊ መብቶችን ማስከበር የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ የሕዝብ ተወካዮች፣ የፍትሕ አካላት፣ ሲቪል ማኅበረሰብ እና ሌሎች አካላት በቅንጅት ሊወጡት የሚገባ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ገልፀዋል።




ባለፉት ጊዜያት ኮሚሽኑ ላከናወናቸው የሰብአዊ መብት መስፋፋት ሥራዎች የቋሚ ኮሚቴዎቹ አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ ሕግ አውጭው ከክትትል ባለፈ ተቀራርቦ መሥራቱና በጋራ መንቀሳቀሱ ውጤት የታየበት በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በበኩላቸው፣ ኢሰመኮ ያስመዘገባቸው ስኬቶች በሁለንተናዊ መልኩ እውን እንዲሆኑ ምክርቤቱ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀው፣ ውጤታማ ትብብርና ለጋራ ዓላማ አብሮ መሥራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።




አቶ እውነቱ “የተመዘገቡት ተጨባጭ ውጤቶች ኮሚሽኑ ከውትወታ ባለፈ ወደ ተፅእኖ ፈጣሪነት እየተሸጋገረ መሆኑን አይተናል ይህንን ማጠናከር ከኮሚሽኑ ይጠበቃል ” ብለዋል።
የዛሬው ውይይት ኮሚሽኑ ከምክር ቤቱ ጋር ሲያካሂዳቸው የነበሩ ተከታታይ ውይይቶችና መድረኮችን የሚያስቀጥል ነው። በዚህ መድረክም ከተለያዩ የምክር ቤቱ መዋቅሮች የቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ጋር በሰብአዊ መብት ጉዳዮች፣ በተቋማት ትብብርና በፓርላማዊ ክትትል ላይ የጋራ ግንዛቤ ይፈጠራል።




በዛሬው መርሃግብርም የኢሰመኮ አዲሱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች የተገኙ ውጤቶች እና ተግዳሮቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
እንዲሁም ኮሚሽኑ፣ ከአፍሪካ ሕብረት (AU) እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) የሰብአዊ መብቶች ተቆጣጣሪ አካላት ምክረ ሐሳቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ በጭብጥ ተከፋፍለው የቀረቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክረ ሐሳቦች ማጠቃለያ (Compendium) ሰነድ በይፋ ለምክርቤቱ አስረክቧል።