የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜያት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) በሰዎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ተከትሎ ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት ተጠያቂነትን ማረጋገጥን ጨምሮ እየደረሰ ካለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ጋር የሚመጣጠን መፍትሔ እንዲሹ የሚያሳስብ መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል። በዞኑ ያለው ሁኔታ ለተወሰኑ ጊዜያት እየተሻሻለ የነበረ ቢመስልም ከጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ታጣቂ ቡድኑ በሽርካ፣ በጉና፣ በመርቲ፣ በአሰኮ እና በኦንቆሌ ዋቤ ወረዳዎች በሰዎች ላይ በፈጸማቸው ጥቃቶች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የደህንነት ሥጋቶች ምክንያት የነዋሪዎች መፈናቀል መከሰቱን ኢሰመኮ የደረሱትን ጥቆማዎችና አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ነዋሪዎችን እና የየአካባቢዎቹን የመንግሥት ኃላፊዎች በማነጋገር ባሰባሰባቸው መረጃዎች ማረጋገጥ ችሏል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በዞኑ ሽርካ ወረዳ ጃዊ ቀበሌ እና በሮቤ ወረዳ ገባ ቀበሌ በፈጸመው ጥቃት ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ቁጥራቸው በውል ባልተለዩ ሰዎች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ አካል ጉዳት፣ እገታ እንዲሁም መፈናቀል መድረሱን ኢሰመኮ በተለያዩ መንገዶች ባሰባሰባቸው መረጃዎች አረጋግጧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎች የሚፈጸመው ጥቃት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እያስከተለ መሆኑን ጠቅሰው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት የሆኑት በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ጉዳቶች፣ ማፈናቀሎች፣ እገታዎች እንዲሁም የንብረት ውድመቶችና ዘረፋዎች የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ጨምሮ ነዋሪዎች በሰላምና በደህንነት የዕለት ተዕለት ተግባራትን እንዳያከናውኑ አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥታት በተደጋጋሚ ጥቃቶች በተፈጸሙባቸው እና የጥቃት ሥጋት ባለባቸው አካባቢዎች በቂ የጸጥታ አካላትን እንዲያሰማሩ እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲያመቻቹ እንዲሁም ተመሳሳይ ጥቃቶችን ቀድሞ የመተንበይና የመከላከል ሥራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።