የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአዲስ አበባ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት ተሐድሶ ማእከል ሠራተኞች ጋር በሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ጥር 23 እና 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ ውይይቱ ሠራተኞች ሰለ ሕፃናት መብቶች እና ሰለመብቶቹ አያያዝ ያላቸውን ዕውቀት እና ክህሎት ለማዳበር ያለመ ሲሆን በውይይቱ ከአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ፣ ከፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ዳኞች ፎረም፣ ከአዲስ አበባ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት የተሐድሶ ማእከል የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችእና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ኢሰመኮ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው በተገኙ ሕፃናት ማቆያና ተሐድሶ ተቋማት ላይ ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተለዩ ግኝቶች፣ እንዲሁም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ዳኞች ፎረም አስተባባሪ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ ትምሕርት ክፍል የሕፃናት መብቶች አያያዝን በሚመለከት ያዘጋጃቸው ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ ሕፃንነት (childhood) እና የሕፃናት እድገት ምንነት፣ ከሕፃናት ጋር የመግባቢያ መንገዶች፣ ሙያዊ ሥነ-ምግባሮች፣ አስተሳሰብ ተኮር የባህሪ ለውጥ ዘዴ፣ ወንጀል እና የወንጀል ባህሪያት፣ የአመራር እና የማማከር አገልግሎት እንዲሁም በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናትን አያያዝ አስመልክቶ በፍርድ ቤት ያሉ ተሞክሮዎች እና ከተሐድሶ ማዕከል ጋር ያለው ቁርኝት የሚያሳዩ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ሥራዎቻቸውን በቅንጅት በመሥራት በተቋሙ ውስጥ ያሉ ሕፃናትን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ከጥቃት ለመከላከል፣ ጤናማ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ለማዳበር፣ ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን እና ሰብአዊ መብቶቻቸውን መሠረት ያደረገ አያያዝን ለማጎልበት እንዲሁም የሕፃናቱን አስተሳሰብ በዘላቂነት ለመለወጥ የሚረዱ ሙያዊ ክህሎቶችን ከግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ እንዳገኙ እና ይህን ወደ ተግባር መለወጥ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት የፍርድ ቤት ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት የመምህራን አስተያየት ተካቶ ለፍርድ ቤት ቢቀርብ የተሻለ መሆኑን፣ እንዲሁም በተቋሙ የጠባይ እርምትና ተሐድሶ ቆይታቸውን ጨርሳው የሚወጡበት ትእዛዝ ሲሰጥ ቤተሰብ አፈላልጎ የማቀላቀያ ጊዜ ታሳቢ ቢደረግ የሕፃናቱን ጥቅምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንደሚረዳ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ቆንጂት ደበላ ኢሰመኮ የሕፃናቱን ሰብአዊ መብቶች ለማስጠበቅ በተሐድሶ ማእከሉ አገልግሎት ለሚሰጡ ሠራተኞች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የክህሎት ማጎልበቻ መድርኮች ሊመቻቹላቸው ይገባል የሚል ምክረ ሐሳብ ሰጥቶ የነበረ መሆኑን አስታውሰው ባላሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በግንዛቤ ማስጨበጫው መድረክ ያገኟቸውን ዕውቀት እና ክህሎት በቀጣይ በክትትሉ የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እና የሕፃናቱን ሰብአዊ መብቶች ለማስጠበቅ በሚረዳ መንገድ ተግባር ላይ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ አና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል ኢሰመኮ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የሕፃናት መብቶችን መጠበቅ እና ማስፋፋት መሆኑን ገልጸው በወንጀል ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት ማቆያ እና ተሐድሶ ማእከላት ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትን መብቶች አያያዝ ለማሻሻል በማእከሎቹ አገልግሎት የሚሰጡ ሁሉም ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ፣ በቁርጠኝነት እና በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።