የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአሳሳቢ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ ከሚገኘው የትግራይ ግጭት ጋር በተገናኘ የተፈጸሙ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ማድረስ፣ ግድያ፣ ዘረፋ እና መፈናቀል በተመለከተ ምርመራ ለማካሄድ ወደ አማራ ክልል አካባቢዎች የባለሙያ ቡድን ይልካል ። ኮሚሽኑ ነሐሴ 13 ቀን 2013 ከሰዓት በኃላ በክልሉ ደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ከተማ ላይ በሕወሃት ታጣቂዎች እንደተፈጸመ በተነገረ የከባድ መሳሪያ ድብደባ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑት ውዴ ዋሌ (ዕድሜ 50)፣ እሱባለው ድረስ (ዕድሜ 23)፣ አዲሳለም ድረስ (እድሜ 18)፣ ሰርካለም ድረስ (ዕድሜ 26) እና ሕጻን አመል ድረስ (እድሜ 4 ወር) መገደላቸውን አረጋግጧል። በተጨማሪም በሟቾች ግቢ ተከራይተው ይኖሩ የነበሩ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
በመስፋፋት እና በመባባስ ላይ የሚገኘው ግጭት በሲቪል ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እና ሰብአዊ ቀውስን በማስከተል ላይ ነው። ኮሚሽኑ በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ሲቪል ሰዎችን ዒላማ እንዳያደርጉ በድጋሚ ያሳስባል።