የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከየካቲት 2 እስከ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጋናው አቻ የሰብአዊ መብቶችና የአስተዳደር ፍትሕ ኮሚሽን (CHRAJ) በአክራ የልምድ ልውውጥ ጉብኝት አድርጓል። ጉብኝቱ የተደረገው፣ ኢሰመኮ ከጥር ካቲት 27 እስከ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በያውንዴ ካሜሩን በተካሄደው የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (NANHRI) ጠቅላላ እና 15ኛው የሁለት ዓመት ጉባኤ ላይ ከተሳተፈ በኋላ ነው።

የልምድ ልውውጥ ጉብኘቱ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አደሎን እና የጋናው ተቋም (CHRAJ) ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያገናኘ ሲሆን በሁለቱ “ደረጃ-ሀ” (A-status) የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መካከል ያለውን ተቋማዊ አስተዳደር እና የሥራ አፈጻጸም ለማጠናከር ያለመ ነው። የጋናው ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ያለው ጠንካራ የአመራር መዋቅር እና ቀጠናዊ ተሳትፎ ለአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጠቃሚ የትምህርት አጋር እንዲሆን አስችሎታል።

በጉበኝቱ የጋናው የሰብአዊ መብቶች ተቋም ለኢሰመኮ ሥራ ጠቃሚ የሆኑ ተሞክሮዎችን አጋርቷል። ከእነዚህም መካከል የጋናን እ.አ.አ. 2024 የፕሬዝዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫዎችን የተከታተለበት ሂደት፣ የስትራቴጂክ ዕቅድ ክለሳ እና የአምስት ዓመት (እ.አ.አ. ከ2026–2030) ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ የተቋሙ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር የሚደረግ ግንኙነት፣ በንግድ እና ሰብአዊ መብቶች፣ በአቤቱታ የሚቀርቡ ጉዳዮች አያያዝ፣ የተቋሙ ውሳኔዎች አፈጻጸም እንዲሁም ተቋሙ ለሕዝብ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን የተከናወኑ ሥራዎች ይገኙበታል።

ሁለቱም ተቋማት የአምስት ዓመት (እ.አ.አ ከ2026–2030) ስትራቴጂክ ዕቅዳቸውን በማዘጋጀትና በመከለስ ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ እንዲሁም የጋናው ተቋም (CHRAJ) የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (NANHRI) የሊቀ-መንበርነት ኃላፊነት ዘመኑን እያጠናቀቀ ያለ እና ኢሰመኮ ደግሞ ተረካቢ ምክትል ሊቀ-መንበር በመሆናቸው ጉብኝቱ ለሁለትዮሽ ትምህርት ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል።

ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አደሎ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበው፣ ይህ የልምድ ልውውጥ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና በሁለቱም ሀገራት የሰብአዊ መብቶችን መከላከል እና ማስፋፋት ሥራን ለማጎልበት ውጤታማ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።