የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይፋዊ መግለጫ
ሚያዚያ 11 ቀን 2014 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ ጌዴኦ ዞን፣ ዲላ ዙሪያ ወረዳ በሚገኘው ጪጩ ጤና ጣቢያ በወ/ሮ ስምረት ጥላሁን ላይ ተፈጽሟል በተባለ አድሏዊ አያያዝ ሁኔታ ላይ በአካል ወደ ቦታው በመሄድ ከመጋቢት 16 እስከ መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው ምርመራ፣ ወ/ሮ ስምረት ጥላሁን ዓይነስውር በመሆናቸው ያለባቸውን የአካል ጉዳት መሰረት ያደረገ አድልዎ በጤና ጣቢያው ባለሙያዎች የተፈጸመባቸው መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኝነትና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ የምረመራውን መነሻ ሲያስረዱ፣ “በወ/ሮ ስምረት ጥላሁን ላይ የተፈጸመው ከአድልዎ ነጻ የመሆን መብት እንዲሁም የሕጻን ልጃቸውን ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ የማግኘት መብት ጥሰት በአንድ ሰው እና አንድ ሕፃን ላይ የተፈጸመ ቢመስልም ምሳሌነቱ አካል ጉዳተኞችን ሁሉ የሚመለከት መሆኑን” አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑ በምርመራው ከግል ተበዳይ፣ ከተበዳይ ቤተሰቦች፣ ከጤና ጣቢያው ባለሙያዎችና ኃላፊዎች፣ ከዲላ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ተወካይ፣ ከዲላ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት እና አስተዳደር አካላት እንዲሁም ከጌዲኦ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት (ጽ/ቤት) ተወካዮች ጋር ካደረጋቸው ቃለ መጠይቆች እንዲሁም በጤና ጣቢያው በአካል ተገኝቶ ምልከታ በማድረግ ማስረጃዎችን አሰባስቧል፡፡
ወ/ሮ ስምረት ጥላሁን በዲላ ከተማ፣ የሀሴ-ዴላ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፤ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በ 6፡30 ሰዓት አካባቢ የመውለጃ ጊዜያቸው በመድረሱ የቅድመ ወሊድ ክትትል ሲያደርጉበት ወደነበረበት የጪጩ ጤና ጣቢያ በመሄድ በዛው ዕለት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ገደማ ልጃቸውን በሰላም ተገላግለዋል፡፡ በዕለቱ በጤና ጣቢያው የእናቶች ማዋለጃ ክፍል ውስጥ ተረኛ ሰራተኞች የነበሩ ነርሶች ተበዳይን ከሌሎች ሁለት ወላድ እናቶች ለይተው፣ ሰብአዊ ክብርን በሚነፍግ እና ለጤና በማይመች መፀዳጃና መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ከተወለደው ሕፃን ልጃቸው ጋር ለሰዓታት እንዲቆዩ ማድረጋቸውን መረዳት ተችሏል፡፡
ወ/ሮ ስምረት፣ መፀዳጃ ክፍል ውስጥ እንዲተኙ ከተደረገ በኋላ በክፍሉ ውስጥ በነበረው መጥፎ ጠረን ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የሆድ ቁርጠት እና የጤና መታወክ አጋጥሟቸዋል፡፡ የተበዳይ እህት የሆኑት ወ/ሪት መውደድ ጥላሁን ክፍሉ እንዲቀየርላቸው የጤና ጣቢያውን ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ቀና ምላሽ ባለማግኘታቸው ወ/ሮ ስምረት የተኙበትን ክፍል ፎቶ በማንሳት በማኅበራዊ ሚዲያ ለሕዝብ ይፋ አውጥተዋል፡፡ ፎቶው በማኅበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱ ከታወቀ በኋላ በወቅቱ ተረኛ ሰራተኞች የነበሩ ነርሶች ወ/ሮ ስምረትን ከነበሩበት መፀዳጃ ክፍል አውጥተው በጊዜው ወላድ እናቶች ያልነበሩበትና ተቆልፎ ወደነበረ ሌላ የድኅረ ወሊድ ማቆያ ክፍል እንዲዘዋወሩ ማድረጋቸውን ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል፡፡
ወ/ሮ ስምረት በበኩላቸው ከወለዱ በኋላ እንዲያርፉ የተደረገበት ክፍል ውስጥ ያለው መጥፎ ጠረን ከየት የሚመጣ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቤተሰባቸውን ይጠይቁ እንደነበረ፣ ቤተሰብ ግን ሁኔታውን ቢያውቁ ሊሰማቸው የሚችለውን ሥነልቦናዊ ጉዳት ከግምት በማስገባት ምላሽ እንዳልሰጧቸው ገልጸዋል። በቤተሰቡ እና በጤና ባለሙያዎቹ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየከረረ ሲመጣ ግን የትና በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ለማወቅ እንደቻሉ ለኢሰመኮ አስረድተዋል።
ይህ ድርጊት መፈጸሙ ከተሰማ በኋላ የዲላ ወረዳ ዙሪያ አስተዳደር ጽ/ቤት ከወረዳው ፖሊስ እና ዓቃቤ ሕግ ጽ/ቤቶች የተውጣጣ የምርመራ ቡድን በማዋቀር ከመጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ምርመራ እንዲጀመር ማድረጉን ገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት፤ የዲላ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ድርጊቱ እንዲታረም አላደረጉም፣ መረጃም አዛብተዋል በሚል የጤና ጣቢያውን ኃላፊ ጨምሮ ወ/ሮ ስምረት ጥላሁን እና ሕጻን ልጇን በመፀዳጃ ክፍል ውስጥ እንዲተኙ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ሦስት የጤና ጣቢያውን ባለሙያዎች፤ በድምሩ አራት ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውለው ምርመራ ማድረጉን ገልጿል፡፡ በምርመራው ሂደት በዲላ ዙሪያ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት (ፍ/ቤት) ከቀረቡ በኋላም በተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ በቁጥጥር ስር መቆየታቸውንና የዋስ መብታቸው የተከበረላቸው መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ድርጊቱን ተከትሎ ተገቢውን አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ አልወሰዱም ያላቸውን የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ እና ምክትል ኃላፊን ከሥራቸው እንዲታገዱ ማድረጋቸውን፣ “የግል ተበዳይን እና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው፣ ለወ/ሮ ስምረት ጥላሁን የሕጻናት አልባሳትና ምግብ-ነክ ስጦታዎችን” ማበርከታቸውን ገልጸዋል።በተጨማሪም ለወ/ሮ ስምረት የቀበሌ መኖሪያ ቤት በካሳ መልክ ለመስጠት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር እና የጌዲኦ ዞን አስተዳደር አካላት ለኮሚሽኑ አስታውቀዋል፡፡
ኮሚሽኑ በምርመራው ወ/ሮ ስምረት ጥላሁን ላይ ዓይነስውር በመሆናቸው ያለባቸውን የአካል ጉዳት መሰረት ያደረገ አድልዎ የተፈጸመባቸው ስለመሆኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ አግኝቶታል፡፡
ይኽም አካል ጉዳትንም ሆነ ሌሎች ሁኔታዎችን መሰረት ካደረገ ማንኛውም ዓይነት አድልዎ ነጻ የመሆን ሰብአዊ መብታቸውን የጣሰ ድርጊት ነው፡፡ የተበዳይ ሕጻን ልጅም በተወለደበት ወቅት ልዩ የጤና እንክብካቤና ትኩረት የሚያስፈልገው ሆኖ እያለ፤ ለጤና ፍጹም ተስማሚ ባልሆነ የመፀዳጃ ክፍል ውስጥ እንዲተኛ መደረጉ የሕፃኑን የሰብአዊ ክብር እና የልዩ ጥበቃና እንክብካቤ መብቶቹን የጣሰ ድርጊት ነው፡፡
ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ የጌዴኦ ዞን እና የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር አካላት የወሰዱትን ተገቢ ምላሾች አመስግነው፤ “የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የግድ የተጠርጣሪዎችን መታሰር ሳያስፈልግ ተገቢው አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን እንዲከታተሉ፣ ተበዳዮች ተገቢውን ፍትሕ እና ካሳ ማግኘታቸውን እንዲያረጋግጡ” አሳስበዋል።