የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሴቶች መብቶች ላይ ለሚሠሩ መደበኛ ያልሆኑ የሴቶች መብቶች አደረጃጀቶች የግንዛቤ ማሳደጊያ ውይይት በሰኔ 11 እና 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። ውይይቱ መደበኛ ያልሆኑ የሴቶች መብቶች አደረጃጀቶችን ዐቅም በማሳደግ ሥራቸውን ከሰብአዊ መብቶች መርሕ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲያከናውኑ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በዞንና በወረዳ ያቋቋማቸው የበጎ ፈቃደኛ ኮሚቴ አመራሮች፤ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ፣ ከሶማሊ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትና የሰብአዊ መብቶች ምንነት፤ ለጥሰት ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡ አቤቱታዎች አቀባበል፤ የምርመራ ሥነ ሥርዓት መሠረታዊ መርሖች፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የደረሰባቸውን ሴቶች እና ሕፃናት ቃለ-መጠይቅ የማድረግ ስልቶች እና የሥነ-ልቦና ጉዳትን ታሳቢ ባደረገ ምላሽ አሰጣጥ፤ እንዲሁም የአደረጃጀቶቹን አሠራር ለማጠናከርና ለመደገፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ተሳታፊዎች በየአካባቢያቸው የሚከሰቱ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን እና በሥራ እንቅስቃሴያቸው የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶችን አጋርተዋል። የአካባቢ ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብነት፣ መረጃዎችን በአግባቡ አለማደራጀትና የአሠራር ሥርዓት ክፍተቶች፣ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የመቀበል ዐቅም ውስንነት፣ እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምላሽ አሰጣጥ ዙሪያ ውስንነቶች እንደሚታዩ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር አሸነፈች አበበ፤ ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ የሕግ ድጋፍ ለማድረግ ብሔራዊ የነጻ የሕግ ድጋፍ ስትራቴጂን ለማስፈጸም የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅን አጸድቆ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ መደበኛ ያልሆኑ የሴቶች አደረጃጀቶች የሚሰጧቸው የሕግ ድጋፎች በተለይም ለሴቶች እና ለሕፃናት መብቶች መከበር ወሳኝ መሆናቸውን አብራርተዋል። አክለውም እነዚህ አገልግሎቶች ይበልጥ ሊጠናከሩና ሰብአዊ መብቶች ተኮር ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።