የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ጋር በመተባበር በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ላይ ያተኮረ የዐቅም ግንባታ ዐውደ ጥናት ሚያዝያ 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ አካሂዷል፡፡ በዚህ ዐውደ ጥናት የክልሉ ሕግ አውጪ፣ ተርጓሚ እና አስፈጻሚ አካላት፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤን ጨምሮ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና ሌሎች የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።


በዐውደ ጥናቱ የሰብአዊ መብቶች ጽንሰ ሐሳቦች እና መሠረታዊ መርሖች፣ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች፣ የኢሰመኮ ሥልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ መርሖች እና የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫዎች የተዳሰሱ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የቀረቡ ገለጻዎችን ተከትሎ ተሳታፊዎች በዝርዝር ተወያይተዋል።


በውይይቱ የተሳተፉ የክልሉ ልዩ ልዩ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የዐቅም ግንባታ ዐውደ ጥናቱ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመው፣ መሰል መድረኮች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ሠራተኞች ተደራሽ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ሰብአዊ መብቶችን ማስከበርና ማስፋፋት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑንም አጽንዖት ሰጥተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ክብርት ወ/ሮ አስካል አልቦሮ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። አክለውም ምክር ቤቱ በክልሉ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ይበልጥ እንዲጎለብትና ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማስቻል የዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ ፎረም ለማቋቋም ከኢሰመኮ ጋር እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ባለፉት ዓመታት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ የተከሰቱ እና የተባባሱ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በመጥቀስ፣ የጥሰት መንስዔዎችን መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመድረኩ ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር በክልሉ ለሚታዩ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ተግዳሮቶች ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ሰላም ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን በመጥቀስ ለዘላቂ ሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥም አሳስበዋል። በመጨረሻም ክልሎች በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሥር የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ በሀገራዊ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።