የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የዳኝነትና የዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ ለተሳካ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ባካሄደው ሀገራዊ ምክክር ላይ ተሳትፏል። በምክክሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ቴዎድሮስ ምሕረት፣ የኢትዮጰያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኢዲተር መሠረት ዳምጤ እና የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ ሚኒስትሮች፣ የተጠቀሱት ተቋማት ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የክልል ፍርደ ቤቶች ፕሬዝደንቶች ተሳትፈዋል።

በሀገራዊ ምክክር መድረኩ የዳኝነት እና የዴሞክራሲ ተቋማት በተለይም ለተሳካ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ባለፉት 5 ዓመታት ያከናወኗቸውን የለውጥ ተግባራት፣ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች እና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎችአቅርበዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ 3 የጊዜ ወሰኖችን ታሳቢ በማድረግ ኢሰመኮን በተመለከተ ባቀረቡት ገለጻ፣ ኢሰመኮ ከለውጥ በፊት ነጻ እና ገለልተኛ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ያልነበረ፣ ከሰብአዊ መብቶች መርሖች የሚቃረኑ ሕጎች ሲረቀቁና ሥራ ላይ ሲውሉ ዝምታን የመረጠ፣ የተቋሙ አመራርና ባለሙያዎች የዐቅም ውስንነት የነበረባቸው፣ ሪፖርቶቹም በአስፈጻሚው አካል ተጸዕኖ የተነሳ ገለልተኝነትና ተዓማኒነት ይጎድላቸው የነበሩ እና ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ይፋ የማያደርግ መሆኑን አስታውሰዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በለውጥ ሂደት የፓሪስ መርሖችን (Paris Principles) መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/1992 በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 መሻሻሉን ተከትሎ ኢሰመኮ መንግሥትን ጨምሮ ከማንኛውም ሌላ አካል ነጻ እና ገለልተኛ መሆኑ መረጋገጡና ከሰብአዊ መብቶች ጥበቃና ማስፋፋት አንጻር ከሞላ ጎደል የተሟላ ተልዕኮና ኃላፊነት እንዲኖረው መደረጉ፤ በዚህም ኢሰመኮ ተቋማዊ የሰው እና የፋይናንስ ሀብቱን ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር መቻሉ፤ በሰብአዊ መብቶች ማስፋፋት እና መጠበቅ ሥራዎቹ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች አካላት ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆኑ፤ ብቃትና ዐቅም ያለው አመራርና የሰው ኃይል መገንባት መቻሉ፤ ሥራን የሚያቀላጥፉ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች ሥራ ላይ መዋላቸው እና ከመንግሥትና ከአጋር ተቋማት የሚገኘው በጀት መጨመሩ በባለፉት 5 ዓመታት ከተመዘገቡ አንኳር ለውጦች መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።

እነዚህና ተያያዥ ለውጦች በፈጠሩት ምቹ ሁኔታና ዐቅም ኮሚሽኑ በባለፉት 5 ዓመታት ከ8000 በላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አቤቱታዎችን ማስተናገድ መቻሉ፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (United Nations Office of the High Commissioner for Human Rights (UNOHCHR) ጋር በመሆን ያከናወነው የጣምራ ምርመራ ሪፖርትን ጨምሮ ከ60 በላይ ሰፋፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምርመራዎችን በማከናወን ሪፖርቶቹ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርሱ ማድረግ መቻሉ፤ ከUNOHCHR ጋር በመሆን ባከናወነው ምርመራ በተሰጠ ምክረ ሐሳብ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲቀረጽ እና እንዲጸድቅ መደረጉ፤ ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የሚመሩበትን የፓሪስ መርሖች ሙሉ በሙሉ በማሟላቱ በተለይም ኮሚሽኑ በገለልተኝነት ሥራውን ማከናወን መቻሉ፣ በካሄዳቸው ተዓማኒ የሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ ምርመራና ውትወታ ተግባራት እንዲሁም በፈጠራቸው ትስስሮች የደረጃ “ሀ” (“A”-Status) ዕውቅና ማግኘቱ እንዲሁም በቅርቡ የአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (Network of African Human Rights Institiutions (NANHRI) ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በካሜሮን/ያወንዴ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ኢሰመኮ ቀጣዩን ጠቅላላ ጉባኤ እና 16ኛውን ኮንፍረንስ እንዲያዘጋጅ፤ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ደግሞ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የትስስሩ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው መመረጥ መቻላቸው አንደ ቁልፍ ስኬቶች የሚወሰዱ መሆናቸውን ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ የመረጃ፣ የኮሙኒኬሽን እና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት በመዘርጋቱ እና ተግባራት በቴክኖሎጂ እንዲመሩ በመደረጉ የአቤቱታ መቀበያና ማስተናገጃ ዲጂታል ሥርዓት፤ የሰብአዊ መብቶች ምርመራ የሚከናወንበት፣ የተቋሙ ሰነድ የሚከማችበት እና ልውውጥ የሚደረግበት ዲጂታል ዳታቤዝ፤ ለሕዝብ መረጃ የሚያጋራበት ድረ ገጽ፤ በተቋሙ አመራር፣ ባለሙያዎችና አጋር አካላት መካከል መረጃ ልውውጥ የሚደረግበት፣ እንዲሁም የሰው ሀብትና የፋናንስ አስተዳደር ሥራዎች የሚቀላጠፉባቸው ዲጅታል አሠራሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን አብራርተዋል።

በተጨማሪም የኢሰመኮ ነጻነትን፣ ተዓማኒነትን እና ገለልተኝነትን ማጠናከር፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትብብርንና አጋርነትን ማጎልበት፤ አዳዲስ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በመለየት ጥበቃን ማረጋገጥና ማስፋፋት፤ የኮሚሽኑን ተደራሽነት ማረጋገጥ፤ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ማጠናከር እና የሽግግር ፍትሕን፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን እና ሌሎች ሀገራዊ ተነሳሽነቶችን መደገፍ የኢሰመኮ የወደፊት የትኩረት መስኮች መሆናቸው ተመላክቷል። የተቋማቱን ገለጻ ተከትሎም በተካሄደ ውይይት ኢሰመኮ በሀገራዊ አጅንዳዎች ላይ ያለውን አቋም በማስመልከት ለቀረበለት ጥያቄ የሰብአዊ መብቶች ማስፋፋት እና ጥበቃ ላይ ብቻ የሚሠራ መሆኑን በአጽንዖት በመግለጽ ከእነዚህም ጋር ተያያዥነት ባላቸው አጀንዳዎች ላይ በአጋርነት እንደሚሠራ ነገር ግን ነጻነቱን እና ገለልተኝነቱን አደጋ ላይ በሚጥሉ አጀንዳዎች ላይ አስተዋጽዖው የተገደበ መሆኑ ተገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ሁሉም የዳኝነትና የዴሞክራሲ ተቋማት ከሕግ ማዕቀፍ፣ ከሰው ሀብት ልማት እና ከቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት አንጻር በአጠቃላይ በተቋም ግንባታ ላይ በልዩ ትኩረት በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው፤ ለዚህም ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ትብብር እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ በየዘርፋቸው የጀመሯቸውን የለውጥ ሥራዎች በማጠናከር በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ማናቸውም ጉዳዮች በተለይም የዳኝነት እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ከሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጋር የሚመጋገቡ በመሆናቸው ኢሰመኮ ተቋማዊ ነጻነትን እና ገለልተኝነትን ጠብቆ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በአጋርነት የሚሠራ መሆኑን ገልጸው በምክክሩ የተሳተፉ አካላት ሰብአዊ መብቶችን ማእከል ያደረጉ አገልግሎቶችን በመስጠት ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።