የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች በሥራ ቅጥር ሂደት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመፍታት የአካል ጉዳተኞች የሥራ መብት በተሻለ ሁኔታ እንዲከበር ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ ጥር 22 ቀን 2018 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። በውይይቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት፣ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የሥራ እና ክህሎት ቢሮ፣ የርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት እና ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የአካል ጉዳተኞች የሥራ መብቶች ምንነት፣ የመንግሥት ግዴታዎች እና አካል ጉዳተኞች በሥራና ቅጥር ሂደት እያጋጠሟቸው ያሉ መሰናክሎች፣ እንዲሁም ከአካል ጉዳተኞች የሥራ መብት ጋር በተገናኘ ለኢሰመኮ የቀረቡ ተደጋጋሚ አቤቱታዎች እና ሊወሰዱ የሚገባቸው የመፍትሔ አማራጮች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ አካል ጉዳተኞችን ለሥራ ቅጥር ውድድር እንዳይመዘገቡ መከልከል፣ ከተመዘገቡ በኋላ ከውድድር ውጭ ማድረግ እንዲሁም ከተቀጠሩ በኋላ የተመጣጣኝ ማመቻቸት (reasonable accommodation) እርምጃዎችን አለመውሰድ በተደጋጋሚ የሚቀርቡ አቤቱታዎች መሆናቸው ተመላክቷል። በሌላ በኩል፣ በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ሥራ ፈላጊዎች በልዩ ልዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሥምሪት እንዲያገኙ ለማስቻል የወጣው ‘የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት መመሪያ ቁጥር 12/2013’ ላይ የተደረገ የሕግ ዳሰሳ /legal review/ ለተሳታፊዎች ቀርቧል።

መመሪያው አካል ጉዳተኞች ከሥራ መብታቸው ጋር በተገናኘ የሚያጋጥሟቸውን ዐይነተ-ብዙ መሰናክሎች ከግምት በማስገባት የተዘጋጀ እና በተግባርም አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ በአወንታዊነት ተነስቷል። በሌላ በኩል የመመሪያው የተወሰኑ ድንጋጌዎች መብቱን ለሚያጣብብ ትርጉም የተጋለጡ/ መሆናቸው፣ መመሪያው ለውስን የአካል ጉዳት ዐይነቶች ሽፋን መስጠቱ እና ከዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አንጻር ያላካተታቸው የጉዳት ዐይነቶች መኖራቸው እንዲሁም አካል ጉዳተኞች የሚሠሩባቸውን እና የማይሠሩባቸውን የሥራ ዘርፎች የመለየትና የመወሰን ሥልጣን ለቀጣሪ ተቋሙና በየደረጃው ለሚገኙ የሰው ሃብት ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬቶች/ቡድኖች የሰጠ መሆኑ ወጥነት ለሌለው እና መብቱን ለሚያጣብብ አተገባበር በር የሚከፍት መሆኑ በክፍተትነት ተጠቅሰዋል።

ከዚህ በመነሳት በመመሪያው ስለ “አካል ጉዳተኛ” በተቀመጠው ትርጉም ውስጥ ተጨማሪ የጉዳት ዐይነቶችን በግልጽ በማካተት የማያሻማ የመብት ጥበቃን ማረጋገጥ፣ ሌሎች ሕጎችን እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መነሻ ባደረገ ጥናት ላይ ተመሥርቶ አካል ጉዳተኞች የሚሠሩባቸውና የማይሠሩባቸው የሥራ መደቦችን እና የጉዳት ዐይነቶችን መለየት፣ የመመሪያውን አፈጻጸም በተመለከተ ጠንካራ የተጠያቂነት ሥርዓትን መዘርጋት እና የግንዛቤ ማሳደጊያ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ በመድረኩ ተገልጿል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ዳይሬክተር ጥበቡ ኃይሉ የአካል ጉዳተኞች የሥራ መብት እንዲከበር ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ የሚያስፈልግ እንደመሆኑ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ያዘጋጀው የሥራ ሥምሪት መመሪያ አበረታች እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህንን መሠረት በማድረግ ሁሉም ባለድርሻዎች በመመሪያው ላይ የተነሱ ነጥቦችን ከግምት በማስገባትና ተጨማሪ ጥናቶችን በማድረግ መመሪያው የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ይበልጥ በሚያረጋግጥ መልኩ የሚሻሻልበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ አሳስበዋል። አክለውም፣ ኢሰመኮ የአማራ ክልልን ልምድ በመውሰድ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሰል የሕግ ማዕቀፎች በሌሎች ክልሎችም እንዲስፋፋ ለማድረግ የውትወታ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።