የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ጽሕፈት ቤት (Office of the High Commissioner for Human Rights-East Africa Regional Office (OHCHR-EARO)) ጋር በመተባበር በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ዐቅምን ለማሳደግ ያለመ የምክክር መድረክ የካቲት 26 እና 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አካሂዷል። በምክክር መድረኩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተወጣጡ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ የምርጫ ሂደቱን እና በሂደቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያላቸውን ሚና የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች፣ መርሖች እና የሥነምግባር ደንቦች፤ በምርጫ ሂደት ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች፣ የመረጃ አሰባሰብ፣ ሪፖርትና ውትወታ ሥራ እንዲሁም በምርጫ ወቅት የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮሩ መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ግልጽ፣ ተአማኒ፣ የሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ሌሎች ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የተረጋገጠበት፣ ተደራሽ እና አካታች እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ተጠቅሷል። በተለይም የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች በቀጠሉበት ዐውድ ውስጥ የሚካሄድ እንደመሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምርጫው ሂደት ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን እና መጠበቃቸውን ለመከታተልና ለማረጋገጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅት እና ከምርጫ በኋላ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በመከታተል፣ ክፍተቶች ሲኖሩ የዕርምት እርምጃ እንዲወሰድ በማገዝ የምርጫው ሂደት በሕዝብ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በሌሎች ባለድርሻ አካላት ዘንድ የሚኖረውን ተአማኒነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠናዊ ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ፕሮግራም ኃላፊ ጆሴፍ ኑባዱም ምርጫ የዴሞክራሲ ማእከል እና ዜጎች በሀገሪቱ የፖለቲካ እና ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን የመሳተፍ መብት የሚተገብሩበት፣ የመንግሥት ቅቡልነት የሚረጋገጥበት እና ዲሞክራሲን ለማጽናት ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም የምርጫ መብቶች ከሌሎች ሰብአዊ መብቶች ጋር የማይነጣጠሉ መሆናችውን አንስተው፣ በምርጫ ወቅት እስራት፣ እንግልት እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመመዝገብ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን በመሥራት እና ለተጋላጭ ወገኖች ድምፅ በመሆን ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት እና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለው ትብብርና ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለምርጫው የሚደረገው ዝግጅት የሕግ ማዕቀፎችንና የሥጋት ግምገማዎችን ከማጤን ባለፈ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መብቶች ባስጠበቀ መልኩ የክትትል ዘዴዎችን መቀየስ እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም የሀገራዊ ምርጫው የሰብአዊ መብቶች ክትትል በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሕግና የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች የተቀመጡ መመዘኛዎችን ያሟላ መሆን እንዳለበት፤ በምርጫው ሂደት የሚሳተፉ አካላትም ይህን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል ግልጽና የተቀናጀ የድርጊት መርኃ ግብር መቅረጽ እንደሚገባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል።