የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ እና በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎ አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ከየካቲት 18 እስከ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ አካሂዷል። በመድረኩ ከአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ እና ትግራይ ክልሎች የተውጣጡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የሽግግር ፍትሕ እና ምርጫን የሚመለከቱ የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተሳትፎ መብቶች፣ በአሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች፣ ከመፈናቀል በኋላ ሰዎች የሚደርስባቸው ሥነ-ልቦናዊ ጉዳትና ጭንቀት እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚቀርቡ ድጋፎች ላይ ገለጻ ተደርጓል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሽግግር ፍትሕ እና ምርጫ ተሳትፎ ወቅት ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ያላቸውን ልምድ ያካፈሉ ሲሆን፣ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እና ቀደም ሲል ከሽግግር ፍትሕ ጋር በተያያዘ በተካሄዱ ሕዝባዊ የምክክር መድረኮች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የነበራቸው ተሳትፎ በቂ እንዳልነበር አንስተዋል። በመፈናቀል ወቅት ለደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ የሽግግር ፍትሕ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ በምክክር መድረኮች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተሳትፎን ማረጋገጥ እና በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ አስፈላጊ ዝግጅቶች ሊደረጉ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በመፈናቀል ወቅት ስላጋጠሟቸው እና አሁንም እያጋጠሟቸው ስለሚገኙ የሥነልቦና ጉዳቶች እና ስለመቋቋሚያ ስልቶች ለተሳታፊዎች ግንዛቤ የሰጠ ገለጻ የቀረበ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ያላቸውን ልምድ አጋርተዋል።

በመድረኩ ስለ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሁኔታ መገንዘብ የመጀመሪያው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑ የተነሳ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን የመፈናቀል ሰለባ የሆኑ ሰዎች ውስብስብ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሚያልፉና ለሥነ-ልቦና ጉዳቶችች ተጋላጭነታቸውም የሚጨምር በመሆኑ፤ ለተፈናቃዮች በሚደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች ውስጥ የሥነ-ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ በአግባቡ ተካቶ በወቅቱ ሊሰጥ እንደሚገባ ተገልጿል።

የኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የስደተኞች እና የፍልሰተኞች መብቶች የሥራ ክፍል ዳይሬክተር ምሕረተአብ ገብረመስቀል በሀገሪቱ የሕግ የበላይነትን እና ዴሞክራሲን ለማስፈን በሚወሰዱ እርምጃዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ተሳትፎ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችም በሂደቶቹ ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና በተመለከተ ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። አክለውም ኢሰመኮ በሽግግር ፍትሕ ሂደት እና በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው እና ተሳትፏቸው እንዲረጋገጥ አበክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል።