የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። መርኃ ግብሩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ስለ ኢሰመኮ ሥልጣን እና ኃላፊነት እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ክትትል መርሖች፣ በመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎች እና በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ነው።



በመድረኩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ከኢትዮጰያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል እና ከኢትዮጵያ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።



የመድረኩ ተሳታፊዎች ስለ ሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች፤የሃይማኖት ተቋማት ለሰብአዊ መብቶች መጠበቅና መስፋፋት ስላላቸው ሚና እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስጋቶችን መፍትሔ ለመስጠት የሃይማኖት ተቋማት ከኢሰመኮ ጋር በቅንጅት መሥራትና ለችግሮች እልባት መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።




በተጨማሪም መርኃ ግብሩ ኢሰመኮ እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና ሰላም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በጅማ ከተማ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።




የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሐጂ መሱድ አደም የሰብአዊ መብቶችን የማስከበር ኃላፊነት የሁሉም መሆኑን ገልጸው በሀገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል ጉባኤው ከኢሰመኮ ጋር በትብብር ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ የሃይማኖት ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር ያላቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ወደፊት በሰብአዊ መብቶች ግንዛቤና ትምህርትእንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ላይ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።