የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፣ በካፋ እና ቤንች ሸኮ ዞኖች ያለውን የጤና መብት አተገባበር አስመልክቶ ግንቦት 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በቦንጋ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል። በውይይቱ ከካፋ እና ቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያዎች፤ ከጊምቦ፣ ገዋታ፣ ሺሾንዴ፣ ቢጣ፣ ዴቻ፣ ጨና እና ሰሜን ቤንች ወረዳዎች፤ ከቦንጋ ከተማ እና ከሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤቶች እንዲሁም በአካባቢዎቹ ከሚገኙ የጤና ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።


በመድረኩ ኢሰመኮ በክልሉ ካፋ እና ቤንች ሸኮ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች የጤና መብት አተገባበር ላይ፣ በተለይም በአካባቢዎቹ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥን አስመልክቶ ባከናወነው ስልታዊ ምርመራ የተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በአካባቢዎቹ የወባ በሽታ ወረርሽኝ ስርጭት ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የታቆሩ ውሃዎችን ማፋሰስ፣ የኬሚካል ርጭት፣ የክትባት እና አጎበር ስርጭት እንዲሁም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመከናወናቸው በአሁኑ ወቅት በበሽታው የመያዝ ምጣኔ ሊቀንስ መቻሉን ገልጸዋል። በሌላ በኩል በሽታውን ለማከም እና ለመቆጣጠር አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶች እና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት መኖሩ ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።

የኢሰመኮ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚ መብቶች ሥራ ክፍል ኃላፊ ሃዊ አስፋው፤ መንግሥት ወረርሽኞችን በመከላከል፣ በማከም እና በመቆጣጠር እንዲሁም ለዜጎች የሕክምና እንክብካቤ በማቅረብ ረገድ ኃላፊነት እንዳለበት በአጽንዖት ገልጸዋል። አክለውም፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚገኙ ለወባ በሽታ ወረርሽኝ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በሽታውን በዘላቂነት ለመቆጣጠር፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የጀመሩትን የተቀናጀ ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።