የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በኦሮሚያ ክልል የቀድሞ አርሲ ዞን በአዲሱ አደረጃጀት ደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ሲርካ ወረዳ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም. የተፈጸመው ጥቃት ያስከተለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ምርመራ አከናውኗል፡፡
በዚህም መሠረት በዕለቱ በደረሱ ጥቃቶች በሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት የደረሰ መሆኑን ኢሰመኮ በአካባቢው በአካል በመገኘት ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከዐይን እማኞች፥ ከማኀበረሰብ ተወካዮች፥ ከሃይማኖት ተቋማት ኃላፊዎች፤ በሕክምና ተቋማት ሕክምና ከሚከታተሉ ተጎጂዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት መረጃዎችን በማሰባሰብ እንዲሁም የመስክ ምልከታ በማድረግና የዲጂታል የምርመራ (digital investigation) ስልት ተግባራዊ በማድረግ ማረጋገጥ ችሏል።
ኢሰመኮ ባከናወነው ምርመራ በክልሉ ደቡብ ምሥራቅ ዞን ሲርካ ወረዳ፣ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ድረስ በአከባቢው ታጥቆ የሚቀሳቀሰው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራ (በተለምዶ ‘’ኦነግ ሸኔ’’) ታጣቂ ቡድን ወደ ቀበሌው በአራት አቅጣጫ በመግባት በፈጸመው ጥቃት 23 በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ ጸጥታ አካላት፥ 5 የሚሊሻ አባላት እንዲሁም 13 ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለማረጋገጥ ተችሏል። ከተጠቀሱት 13 ሕይወታቸው ካለፉት ሲቪል ሰዎች በተጨማሪ በአካባቢው በታጠቁ ኢመደበኛ በሆኑ ታጣቂ ግለሰቦች 7/ሰባት/ ሲቪል ሰዎች የተገደሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። በተጨማሪም በኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በተፈጸመ ጥቃት በ20 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፤ 21 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ 247 ቤተሰቦች ከአካባቢው ተፈናቅለዋል። ለጊዜው ቁጥራቸው ያልተለዩ የቀንድና የጋማ ከብቶች ተዘርፈዋል።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምሥራቅ ዞን፣ ሲርካ ወረዳ፣ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ ባደረገው ምርመራ በአካባቢው ግለሰቦች ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ታጥቀው በስፋት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ችሏል።
ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል፣ የቀድሞ አርሲ ዞን፣ በአሰኮ፣ በአንቆሎ ዋቤ፣ በጉና እና በመርቲ ወረዳዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ጥቃቶችን በተመለከተ፣ መንግሥት ጥቃቶቹን ለመከላከል፣ የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ጥቃት ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ ማሳሰቡ ይታወሳል። መንግሥት የሕይወት፣ የንብረት፥ የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብቶችን የማክበር፣ የመጠበቅና የማሟላት ኃላፊነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13(1) መሠረት በሁሉም የፌዴራልና የክልል የመንግሥት አካላት ላይ የተጣለ ግዴታ ሲሆን ጥሰቶችን ከማጣራትና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ የሚያስችሉ ዘላቂ የመከላከል እርምጃዎችን መውሰድም ይጠበቅበታል። እንዲሁም ከመንግሥት የጸጥታ አደረጃጀት ውጭ ያሉ ኢመደበኛ የታጠቁ አካላትን በተመለከተ አስፈላጊውን ክትትል ሊያደርግ ይገባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በነዋሪዎች ላይ የደረሱት ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል እጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጸው መንግሥት በጥቃቱ የተጎዱና ተመሳሳይ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች ሁሉ በቂና ውጤታማ የሆነ ጥበቃ ሊያደርግ፤ በተለይም የአካባቢው የጸጥታ አካላት አደረጃጃቶችን በመገምገም እና በማስተካከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን በማጠናከር ለሚከሰቱ ስጋቶች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የነዋሪዎች የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና፣ ንብረት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አክለዉም በጥቃቱ ለደረሰዉ ጉዳት ፈጣን ገለልተኛና ውጤታማ ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ፣ ለሟቾች ቤተሰቦች እና ለተገጂዎች አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርግ፤ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የሚያስችል እንዲሁም ተጎጂዎችን ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችሉ አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወስድ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምሥራቅ ዞን በተለያዩ ወረዳዎችና ጊዜያት የተፈጸሙ ጥቃቶች ያስከተሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና መንስዔዎች በተመለከተ ሲያከናዉን የቆየውን ሥልታዊ ምርመራ እያጠናቀቀ ሲሆን የምርመራ ሪፖርቱ ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርግ ይሆናል። እንዲሁም ኮሚሽኑ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና ሶማሊ ክልሎች አዋሳች ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እንዲሁም በትግራይ ክልል ከተካሄደው ግጭት ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልክቶ ምርመራና ክትትል እያደረገ ይገኛል።