የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ማዕከላት ለስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚሰጡትን አገልግሎት ተደራሽነት አስመልክቶ መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል። የምክክር መድረኩ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ነጻ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ወቅታዊ የሥራ ሁኔታን መረዳት፣ በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና እድሎችን መለየት እና ለወደፊት በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ያለመ ነው።

በውይይቱ ከአዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ፣ አሶሳ፣ ደባርቅ፣ ጋምቤላ፣ ጅግጅጋ፣ መቐለ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ማዕከላት፣ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (UNHCR) እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ኢሰመኮ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ፍትሕ የማግኘት መብትን አስመልክቶ ባከናወናቸው የክትትል ሥራዎች የተለዩ ቁልፍ ግኝቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቋንቋ ችግሮች፣ የመረጃና የግንዛቤ ክፍተት እንዲሁም የፍርድ ቤቶች እና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ በቅርበት አለመገኘት እንደ ዋና ተግዳሮት ተጠቅሰዋል። በተለይም ለነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚመደበው በጀት መቀነሱ እንደ ተንቀሳቃሽ ፍርድ ቤቶች ያሉ አገልግሎቶች ቀጣይነት እንዳይኖራቸው ማድረጉ በአሳሳቢነት ተነስቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የበጀት እጥረት፣ በተቋማት መካከል ያለው የሥራ ትብብር ጠንካራ አለመሆን፣ የሕግ ድጋፍ ሰጪዎች የዐቅም ውስንነት እና አገልግሎቱ በሁሉም አካባቢዎች እኩል ተደራሽ አለመሆን እንቅፋት መሆናቸውን ጠቁመዋል። በተለይም ለተፈናቃዮች የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆን እና ፍላጎቶቻቸውን የሚወክሉ የተደራጁ መዋቅሮች አለመኖራቸው ለነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ ተደራሽነት ማነቆ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል እንደ የስደተኛ-መር ማኅበራት መጠናከር፣ የዲጂታል መታወቂያ መስፋፋት እና በተቋማት መካከል የጋራ ኮሚቴዎች መቋቋም ያሉ አበረታች ጅማሮዎች ቢኖሩም፣ አጠቃላይ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ተጨማሪ የተቀናጁ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉ ተመላክቷል።

የኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ምሕረተአብ ገብረመስቀል ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የፍትሕ እና የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በተቋማት መካከል ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ተለዋዋጭና ውስብስብ በመሆናቸው፣ የሚሰጠው ምላሽ ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።