የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ያላቸውን ተደራሽነት፣ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠር እና የባለድርሻ አካላትን ሚና ለመለየት ያለመ የውይይት መድረክ ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል።




በመድረኩ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን፣ ከከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት፣ ከሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም ከታክሲ ማኅበራት እና ከተርሚናል ኢንተርፕራይዝ የተወጣጡ ተወካዮች እና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።




በውይይቱ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እና አዎንታዊ ሁኔታዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን አጠቃቀም ምቹ የሆኑ መሣሪያዎች የሌላቸው መሆኑ፣ መሣሪያዎቹ ባላቸው ጥቂት ተሽከርካሪዎች ላይም በብልሽት ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ መሆኑ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ተደራሽ የአውቶቡስ ማቆሚያዎች እና የእግረኛ መንገዶች አለመኖር፣ በድምጽ ወይም በምስል የሚተላለፉ መረጃዎች እና ጠቋሚ ምልክቶች አለመሟላት፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ቅድሚያ የመስጠት እና ድጋፍ የማድረግ አሠራር ተግባራዊነቱ በግለሰቦች በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ እንዲሁም ከአመለካከት ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ተግዳሮቶች መሆናቸው ተመላክቷል።
በሌላ በኩል የትራንስፖርት አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችሉ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና መመሪያዎች መኖራቸው፣ ለአካል ጉዳተኞች የተለዩ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች (ፓርኪንግ) በዝግጅት ላይ መሆናቸው፣ እንዲሁም አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ተገቢውን የተደራሽነት መስፈርት ያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ፖሊሲ በዝግጅት ላይ መሆኑ በውይይቱ በአዎንታዊነት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።



በተጨማሪም የውይይቱ ተሳታፊዎች የትራንስፖርት አገልግሎትን ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ተደራሽ ለማድረግ የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢሰመኮ ምርመራ እና ክትትል ሥራ ክፍል የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሴፍ ግርማ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የትራንስፖርት አገልግሎት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስበዋል። አክለውም አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን በትራንስፖርት ዘርፍ ለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች እልባት ለመስጠት፤ በጅምር ላይ ያሉ የፖሊሲ ዝግጅት እና መሰል ሥራዎች ተጠናቀው ተግባራዊ እንዲደረጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡