በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ የተመራ 8 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ልዑክ፣ ከጥቅምት 2 እስከ 6 ቀን 2019 ዓ.ም. በሲሪላንካ የልምድ ልውውጥ እያደረገ ይገኛል።
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ እየዘረጋች ላለው ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ከሲሪላንካ ተሞክሮዎችን ለመውሰድ ያለመ ሲሆን፣ የልምድ ልውውጡ ዋና ትኩረትም ሲሪላንካ ከበርካታ አሥርት ዓመታት ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት በኋላ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት ያደረገቻቸውን ጥረቶችና ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች መመልከት ነው።


በዚህም መሠረት በግጭት ወቅት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ የመፈናቀልና የተፈናቃዮች አያያዝ፣ እንዲሁም ተጠያቂነትን በማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን በመገንባት በኩል ያሉ ውስብስብ ሁኔታዎች በሰፊው ይዳሰሳሉ።
በዚህ የጉብኝት መርሃ ግብር ወቅት የልዑካን ቡድኑ ከሲሪላንካ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከጉዳት ማካካሻ መሥሪያ ቤት (Office for Reparations) እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት እና ከፍርድ ቤት አሠራሮች ጋር ይተዋወቃል።


በተጨማሪም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከሲቪል ማኅበራት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች (ICTJ, LAW እና AJAR) ጋር በመመካከር፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የተጎጂዎችን ድምፅ ማዕከል ባደረገ መልኩ በሚከናወኑበት ሁኔታ ላይ ውይይት ያደርጋል።
በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የኢሰመኮ የሽግግር ፍትሕ ሥራ ክፍል ዳይሬክተርና አስተባባሪ፣ የጅግጅጋና የጅማ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተካተዋል።

የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ በልምድ ልውውጡ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ ቋንቋዎች ያሏት፣ ልክ እንደ ሲሪላንካ ጥልቅ ማኅበራዊና ባህላዊ ብዝሃነት ያላት ሀገር መሆኗን በመግለጽ አገራችን ኢትዮጵያ በኤፕሪል 2024 እ.ኤ.አ. የጸደቀችውን ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝና ለዚህም ጠንካራና ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረጉ ተቋማዊ ስልቶች እንደሚያስፈልጓት በማመን ስራዎች እይተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።
ኮሚሽነሩ አያይዘውም የልዑክ ቡድኑ ከዚህ ጉብኝት የሚያገኘውን ልምድ በመቀመር የሀገሪቱን የሽግግር ፍትሕ ሂደት የበለጠ አሳታፊ፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥና ብሔራዊ ዕርቅን የሚያመጣ ለማድረግ እንደ አስፈላጊ ግብአት ይጠቀምበታል በማለት ገለጸዋል፡፡