የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (Network of African National Human Rights Institutions (NANHRI)) ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያለውን የሲቪክ ምኅዳር ለማስፋት እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃን ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ ሚያዝያ 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። በምክክሩ ከተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ (Office of the High Commissioner for Human Rights-East African Regional Office (OHCHR-EARO))፣ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ የሰላም እና ጸጥታ ክፍል፣ ከዴንማርክ ሰብአዊ መብቶች ኢንስቲትዩት (Danish Human Rights Instittion – DHRI)፣ ከኬንያ ሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ ኮሚሽን (Kenya National Commission for Human Rights – KNCHR) እና ከተለያዩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በምክክሩ የሲቪክ ምኅዳርን እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሕግ ማዕቀፎች እና መመዘኛዎች ላይ ያተኮሩ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በተጨማሪም ኢሰመኮ ክትትል፣ ጥናት እና ሕዝባዊ መድረክ (Public Inquiry) በማከናወን እንዲሁም ሞዴል ሕግ በማዘጋጀት የሲቪክ ምኅዳሩን ለማስፋት እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች መብቶችን ለማስጠበቅ ሲያከናውን የቆያቸው ተግባራት በመድረኩ ቀርበዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ የተሻለ የሲቪክ ምኅዳር ለመፍጠር የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች በአካል እና በበይነመረብ (Online) የመብቶች ጥሰት እንዳይደርስባቸው በቂ ጥበቃ መስጠት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (Network of African National Human Rights Institutions (NANHRI)) ዋና ዳይሬክተር ጊልበርት ሰቢሆጎ (Gilbert Sebihogo) የሲቪክ ምኅዳርን ለማስፋት እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃን ለማጠናከር የመንግሥት ቁርጠኝነት እንዲሁም የኢሰመኮ እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር መቅደስ አመኑ የመደራጀት፣ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመረጃ ነጻነት መብቶች መከበር የሲቪክ ምኅዳርን ለማስፋት እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተው የሲቪል ማኅበረብ ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።