የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በትግራይ እና በአፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ግጭቶች በሰብአዊ መብቶች ላይ እያስከተሉ የሚገኙትን ጉዳቶች በቅርበት በመከታተል ላይ ይገኛል።
ኢሰመኮ በትግራይ ክልል ሲፈጸሙ የነበሩ ወጣቶችን አስገድዶ ወደ ውትድርና የማዝመት እርምጃዎች እና የዜጎች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የሚደረጉ ገደቦች እንዲሁም በክልሉና አጎራባች ክልሎች መካከል የሚከሰቱ ውጥረቶችና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ እንዲቆሙና፤ ሁሉም ችግሮች በሰላማዊ ውይይትና በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ጥሪውን ሲያቀርብ የቆየ መሆኑ ይታወሳል። ሆኖም በእነዚህ አካባቢዎች የነበረው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲባባስ ቆይቶ አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ ግጭቶች የተቀሰቀሱና እየተካሄዱ መሆኑን ኢሰመኮ ባሰባሰባቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎች አረጋግጧል። በተለይም እነዚህ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በትጥቅ ግጭት የተጎዱ እና በበቂ ሁኔታ ያላገገሙ በመሆናቸው የትጥቅ ግጭት ዳግም መከሰቱ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ላይ ተደራራቢ ጉዳትን ሊያሳድር የሚችል በመሆኑ እጅግ አሳሳቢ ነው።
ራሱን “ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)” ብሎ የሚጠራው ቡድን ባሰማራቸው ታጣቂዎች፣ በአፋር እና አማራ ክልል ባሉት አዋሳኝ አካባቢዎች ዘልቆ በመግባት መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም. ከለሊቱ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ ጥቃት መክፈቱን፤ በተመሳሳይ የትግራይ ክልል ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው የዋግ ኸምራ ዞን አካባቢዎች እና በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና ‘ሕወሓት’ ባሰማራቸው ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች የተከሰቱ መሆኑን ኢሰመኮ ለመገንዘብ ችሏል።
ግጭቶቹ የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብቶች እንዲሁም የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ሲሆን፣ ለአብነት በትግራይ ክልል የሚገኙ የመቐለ አሉላ አባ ነጋ፣ የሽረ እና የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያዎች ‘ሕወሓት’ ባሰማራቸው ታጣቂዎች ከመስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ በመያዛቸው በረራዎች በመቋረጣቸው በሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት ላይ ተጽዕኖን አሳድረዋል። እንዲሁም ከትግራይ ክልል ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በየብስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ለሙሉ በመቋረጣቸው ምክንያት በመሠረታዊ ቁሳቁሶችና አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ክፍተቶች በመፈጠራቸው፤ ይህንንም ተከትሎ የዋጋ ንረት መከሰት መጀመሩ ተጠቃሽ ናቸው።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሀኑ አዴሎ የተቀሰቀሰው ግጭት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው፣ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች በተለይም የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚ አካላት ስምምነታቸውን እንዲያከብሩ እና በሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎችና ውሳኔዎች በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች የተጣለባቸውን ግዴታዎች በማክበር በተለይም የሲቪል ሰዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ለጉዳት ከሚዳርጉ እርምጃዎች እንዲታቀቡ አሳስበዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ወደ ውይይት እንዲመለሱ ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።